ጥንታዊ የወርቅ ቤተ መንግስት

Spread the love

ጥንታዊ የወርቅ ቤተ መንግስት ነው፡፡ የሰው ልጅ በህይወቱ መሬት ላይ ሲኖር ሊያየው ይገባል የሚባልለት ቅንጡ ጥንታዊ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ፡፡

76 አፓርትመንት ቤቶች እና ዙፋን አዳራሾችን አሟልቶ የያዘ ሲሆን የቃጠሎ አደጋ ደርሶበት እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1992 እንደገና ለምረቃ የበቃ በወርቅ የተለበጠ ቤተ መንግስት ነው፡፡

በውስጡ እጅግ ቅንጡ የሆነና ንጉሱ ባለሟሎቻቸውንና ሚኒስትሮቻቸውን የሚሰበስቡበት እጅግ ትልቅና ልዩ እንደሆነ የሚነገርለት የንጉሱ ልዩ ዙፋን አዳራሽ /ቲሃታን ትሮን ወይም በልዩ መጠሪያው አንበሳ ዙፋን እየተባለ የሚጠራው የቤተ መንግስቱ ክፍል አንዱ ነው፡፡

ለአይን በሚያጸባርቅ የወርቅ ቋሚዎች ያማረው ይህ ዙፋን በርካታ የዓለም ጎብኝዎች ለጉብኝት ሄደው ለማየት የሚጓጉለት ነው፡፡  

ካንባውዛታዲ ቤተ መንግስት ተብሎ ይጠራል፣ በሀገሪቱ ሌሎች አብያተ መንግስታት ቢኖሩም ይህ እጅግ ልዩ ነው፡፡ በቀድሞዋ በርማ የአሁኗ ማይንማር ባጎ በተባለ አካባቢ የተገነባ ሲሆን የአሁኗን በርማ፣ ታይላንድ እና የተወሰነ የቻይና ክፍልን ያስተዳድሩ በነበሩት እና በርካታ ነጭ ዝሆኖች እንደነበሯቸው በሚወራላቸው በንጉስ ባይናውግ ትዕዛዝ እንደ አውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር በ1556 የተገነባ ወርቃማ ቤተ መንግስት ነው፡፡

ከ1 ነጥብ 2 ስኩየር ኪሎሜትር በላይ በሆነ ስፍራ ላይ ያረፈው ጥንታዊው ቤተ መንግስት የተሰራበት የወርቅ መጠን ትክክለኛ መረጃ ባይገለጽም በብዙ ሺ ቶን እንደሚመዘን ይገመታል፡፡ 

167 ግዙፍ በቀላሉ ሊበሰብሱ እና ሊበሉ የማይችሉ ቋሚ ምሶሶዎች ያሉት ቤተ መንግስቱ 135 የሚሆኑት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በስጦታ በተበረከቱ ሰዎች ስም፣ በአካባቢ መጠሪያ እንዲሁም በትንንሽ ከተሞች ሰም በሞን ቋንቋ የተጻፈባቸው ሲሆን በወርቅ የተለበጡና እጅግ ግዙፍ የሆነውን የወርቅ ጣሪያ ደግፈው የያዙ ናቸው፡፡

የንጉሱ የወርቅ ዙፋን እና የወቅቱን ሁኔታ የሚገልጹ ማስታወሻዎች፣ ታሪካዊ ጽሁፎችና መገለጫዎች ለእይታ ክፍት ሆነው በሚሊየን የሚቆጠሩ ጎብኝዎች ከመላው ዓለም ወደ ማይናማር ሲያመሩ ሳያዩት አይመለሱም፡፡

ሌላኛውና በወርቅ ተንቆጥቁጦ የተሰራው የቤተ መንግስቱ አካል ባሃማያርታና ዙፋን ወይን ንብ ዙፋን ሲሆን የንጉሱ የግል ጉዳዮች የተቀመጡበትና ለቤተሰብ ብቻ የሚታዩ እቃዎች የሚቀመጡበት እንዲሁም ልዩ መኝታ ቤትን የያዘ ነው፡፡

የቤቶቹ ጣሪያ በበርማ የቡድሃ ባህል መሰረት ከሶስት እስከ ሰባት ደረጃ ወይም በተለምዶ ጎደሎ ቁጥር ያለው ጣራ ይወደዳል፤ ለዚህም በ7 ደረጃ የተሰራ ጣሪያ ያለው፣ እነዚህ ጣሪያዎችም ከአየር ሁኔታ ጋር የተስማሙ ፣ ከፍሳሽና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ እጅግ ምቹ እና ድምጽ የማያስላልፉ ናቸው፡፡

ይህ ወርቃማ ቤተ መንግስት በተለያዬ ዲዛይን በወርቅ የተለበጡ 9 የንጉስ ዙፋኖች ያሉት ሲሆን የተለያዩ ምክንያቶችም እንዳሏቸውም ይነገርላቸዋል፡፡ ከአንበሳ ዙፋን ውጭ ያሉት ግን አብዛኞቹ በእሳት ቃጠሎ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሲገለጽ በአሁኑ ወቅት በያንጎን ብሔራዊ ሙዝየም ለእይታ ክፍት የሆነውም ይሄው አንበሳ ዙፋን ነው፡፡

በዚሁ ቤተ መንግስት ከስረኛው ክፍል የሚገኘው ናዳውያ የተሰኘው የጥናትና ምርምር ሙዝየም የዚህን ወርቃማ ቤተ መንግስት ቁሳቁሶች ለእይታ ክፍት አድርጎ ያስጎበኛል፡፡

ወደ ማይናማር ባጎ የሚያመራ ሁሉ በዚህ ድንቅ ሙዝየም የጽሑፍ ስራዎችና መዛግብት፣ የንግድ ስራ መለኪያ ሚዛኖች፣ ሰረገላዎች፣ ጥንታዊ ሳንቲሞች፣ አብረቅራቂ ገንቦዎች፣ ጎራዴዎች እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ይገኛሉ፡፡ ይህ ሙዝየም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በ ሞን፣ ሲያሜዝ እና በርማ ቅርጽ የተሳሉ የቡድሃን እምነት የሚያንጸባርቁ ምስሎች ይዟል፡፡

ጣሪያው እጅግ በሚያማምሩ ወርቅ ቅብ ወራጆችና መጋጠሚያዎች ያሉት ቤተ መንግስቱ በቋሚዎቹ ምሶሶዎች መጋጠሚያ ቦታዎች የተለያዩ ዲዛይኖች የተሰሩላቸው ናቸው፡፡

ወደ ላይ ቀጥ ብለው የቆሙት ልዩ የማይንማርን ወግና ባህል የሚያሳዩት እነዚህ የቤተ መንግስቱ ወርቃማ ጉልላቶች ልዩ ውበት ያላቸው ናቸው፡፡ ዙሪያውን ያሉት ሰው መሰል ቅርጾች ለዚህ አስደናቂ ስፍራ ተጨማሪ ውበት የሰጡት ሲሆን የሚጨሱ ማዕጠንቶችም ሌላኛው ገጽታ ነው፡፡

ይህ ታሪካዊ ስፍራ እጅግ በሚያማምሩ ዛፎች የተከበበ እና ተፈጥሯዊነቱን እንዲጠብቅ ተደርጎ የተያዘ ሲሆን መንፈስን የሚያድስ ልዩ ስፍራ ነው፡፡

ይህ ታሪካዊ ቤተ መንግስት ከጥንታዊቷ ያጎን ከተማ ጋር የተሳሰረ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ሀብቷ ነው ለማይናማር፡፡   በግቢው ውስጥ ጥንታዊ የመድፍ ቅርሶች የሚታዩበት ይህ ቤተ መንግስት አስገራሚ የተባለለት የሀገሪቱ የጉብኝት ስፍራ ነው፡፡

ከ40 በላይ እጅግ አስገራሚ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ባሏት የእስያዋ ማይናማር በርካታ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉባት ሀገር ነች፡፡

ከ90 በመቶ በላይ ህዝቧ የቡድሂስት እምነት ተከታይ በሆነባት ማይንማር ወደዚህ ቤተ መንግስት ለመግባት ጫማ ማውለቅና በባዶ እግር መራመድ እንደ ታላቅ ክብር የሚቆጠርና ኃይማኖታዊ ስነስርዓትም ነው፡፡

በሌላ በኩል ወደ ቤተ መንግስቱ ባጎ ሲገቡ ትልቅ የገበያ ማዕከል ተገነባለት ሲሆን በዚህ ማዕከልም ወደ ቤተ መንግስቱ ለመግባት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ለመግዛትና ጎብኝዎች የማይንማር መገለጫ ቁሳቁሶችን ለመሸመት እንዲያስችላቸው የሚረዳ ነው፡፡

በበርካታ ስፍራዎች የቡድሂዝም ወርቃማ ቀለም ያላቸው የአምልኮ ስፍራዎች ወይም በጥቅል ስማቸው ፓጎዳስ የተገነቡባት በመሆኑ ማይንማር ወርቃማ መሬት/ጎልደን ላንድ እስከ መባል ደርሳለች፡፡

ካንባውዛታዲ ቤተ መንግስት ወይም ወርቃማው ቤተ መንግስት በርካቶች የሚጎበኙት ስፍራ ሲሆን በጥቅምት ወር/2024 ብቻ በ10 ሺ የሚቆጠሩ ጎቱሪስቶች እንደጎበኙት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ማይንማር ጥንታዊ አብያተ መንግስታቷ ብቻ ሳይሆን አሁን በርዕሰ ከተማዋ ናይፒዳው የሚገኘው ቤተ መንግስትም ከሚያምሩ አብያተ መንግስታት መካከል የሚጠቀስ ስለመሆኑ ይነሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *