
አልማራይ- የበረኃው ወተት ቋት
በአረብኛው ግጦሽ መሬት በላቲን ደግሞ መመገብ የሚል ፍች አለው፡፡ ይህ ቃል የግዙፉ እንስሳት እርባታ ማዕከል መጠሪያ ነው፡፡ መገኛው ደግሞ ምንም ወንዝ የሌላት እጅግ በርሃማዋ የመካከለኛው ምስራቅ ሰፊ ሀገር ሳኡዲ አረቢያ ነው፡፡
እድሜ ለስራ ትጋት እድሜ ለቴክኖሎጂ አልመራይ በዓለም እጅግ ግዙፉ የእርባታ ማዕከል ለመባል የበቃ ወተት እንደ ወንዝ የሚወርድበት፣ ስጋ እንደጎመን የሚቆረጥበት፣ እንቁላል እንደ አሸዋ የፈሰሰበት መንደር ሆኗል፡፡
አልመራይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1977 ዓ.ም በሁለት የአየርላንድ ወንድማማቾች እና በሳኡዲው መሀመድ ቢን ሳኡድ አልካቢር የተቋቋመ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ በትንሽ አሴት የተቋቋመው ይህ ባለተስፋ ተቋም ለአካባቢው አርሶ አደሮች ወተት በማምረት እንዲያከፋፍሉ ላማድረግ በ300 ላሞች ነበር ስራውን የጀመረው፡፡
ከ28 ዓመታት በኋላ በ2005 ከግል ኩባንያነት ወደ ባለድርሻ ተቋምነት በማደግ ድርሻ በመሸጥ በርካታ አካላት የድርጅቱ ባለቤት እንዲሆኑ ያደረገው ኩባንያው 30 በመቶ የሚሆነውን ድርሻም በሳኡዲ አረቢያ ስቶክ ገበያ ለሽያጭ አቅርቧል፡፡

ከዓመት በኋላም ከወተት ባለፈ ሌሎች የወተት ውጤቶችን ለገበያ በማቅረብ በመላው መካከለኛው ምስራቅ ማስተዋወቁን ተያያዘው፡፡ የሚያቀርበው የአይብ አይነትም እጅግ ተመራጭና ምንም ያልተጨመረበት ጠጣርና ተፈጥሯዊ መሆኑ ደግሞ ልዩ አደረገው፡፡
በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ፓኪስታንና ሌሎችም ሀገራት በመሄድ ተመሳሳይ ስራ ከሚሰሩና የጭማቂ ምርት ከሚያመርቱ እንደ አይ ዲ ጄ ያሉ ኩባንያዎች ጋር ድርሻ የመግዛትና አብሮ የመስራት ውል ተፈራርሟል፡፡
አልማራይ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2011 በኋላ በፍጥነት ያደገበት ወቅት ሲሆን ከግብጹ ፔፕሲኮ ኩባንያ ጋር በመሆን በሀገሪቱ የግብርና ኢንዱስትሪ ከ345 ሚሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በአርጀንቲና ፎንዶሞንቴ የተሰኘ ኩባንያም ስለመግዛታቸው ነበር የተሰማው፡፡
በፍጥነት እየሰፋ የመጣው ይህ የእንስሳትና ተዋጽኦ ምርቶች ኩባንያ አልማራይ በ2014 የባህረ ሰላጤው ሀገራትን የወተትና ወተት ምርቶች ፍላጎት 44 በመቶ ድረስ ተቆጣጠረ፡፡
ከ8 ዓመታት በፊትም ድርጅቱ ያሉት ሰራተኞች 38 ሺ መድረሳቸው አጃኢብ አሰኝቷል፡፡ በ2016 በአሜሪካ በተለይም በካሊፎርኒያ ሰፊ የወተትና ወተት ተዋጽኦ ምርቶች ማምረቻ ቦታ የገዛው አልማራይ በአጠቃላይ 14 ሺ አክሬ ቦታ ስለመያዙም ተነግሮለታል፡፡
ያሳኡዲ አረቢያው ሶቨሬይን ዌልዝ ፈንድ ያለውን የድርሻ መጠን ወደ 16 በመቶ ከፍ ሲያደርገው የኢንቨስትመንት መጠኑም 2 ነጥ 4 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ብሉምበርግ አስነብቧል፡፡
እስካለፈው ዓመት ድረስ ለተከታታይ አራት ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ እጅግ ሰፋፊ የማምረቻ መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ተጠምዶ ከርሟል፡፡

ዋናው ማዕከል ከዋና ከተማዋ ሪያድ በ60 ማይል ርቀት አል ክሃርጂ የሚገኘው የአልማራይ እርባታ ማዕከል የወተት፣ የዳቦ እና የጭማቂ ማቀነባበሪያ ማዕከል አለው፡፡
በበረሃማው አልክሃርጂ አንዲት ላም በቀን እስከ 300 ሊትር ውሃ የመጠጣት ፍላጎት ያላት ሲሆን በቴክኖሎጂ በመታገዝ ከ50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የነበረውን ሙቀት ወደ 21 ዲግሪ ሴልሺየስ የመቀየር አቅም እንዳለውም ይነገራል፡፡
አልማራይ በአሁኑ ወቅት 195 ሺ ላሞች ያሉት ሲሆን ከአንድ ላም እስከ 40 ሊትር ወተት በቀን እንዲሁም በአጠቃላይ በቀን ከ193 ሺ ሊትር እንዲሁም በዓመት እስከ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ሊትር ወተት በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ይህም ከኖርዌይ ሀገራዊ ምርት በላይ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ወተት፣ እርጎ፣ ጭማቂ፣ የዳቦ አይነቶችን፣ እንቁላልና እንቁላል ተዋጽ እንዲሁም የህጻናት ወተትን/ፎርሙላ በየዓይነቱ ለዓለም የሚያቀርበው አልማራይ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ9 ቢሊየን ዶላር በላይ ሀብት እንዳለው ታውቋል፡፡
27 በመቶ የሚሆነውን ምርት ወደ ውጭ የሚልከው አልማራይ 20 ወደ ሚሆኑ የዓለም ሀገራት ምርቱን እንደሚልክ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እንደ ግብጽ፣ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኦማንና ዮርዳኖስ ባሉ 7 ሀገራት ብቻ ከ220 ሺ በላይ የችርቻሮ ሱቆች እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

አልማራይ በዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን ለእንስሳት መኖ የሚሆን ምግብ ከውጭ ሀገራት የሚያስገባ ሲሆን ከ850 ሺ በላይ አእዋፋት ያሉት ሲሆን ከ50 ሺ በላይ የሚሆኑት ዶሮዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጣቢያው የዶሮ፣ የዳክዬ፣ የጉዝ፣ የጊኒ ፎውል፣ የዝየ እና የሌሎችም አእዋፋት ዝርያዎች እርባታ ይናወናል፡፡
ለአልማራይ የሳኡዲ ኢንቨስትመንት ፈንድ የድርጅቱን 16 በመቶ ድርሻ በመያዝ በተለይም ለተቋሙ መጠናከር የላቀ ድጋፍ ሲያደርግለት እዚህ ደርሷል፡፡ አልማራይም ለህጻናት የሚቀርቡትን ወተት ምርቶች በአነስተኛ ዋጋ በመሸጥ፣ የሳኡዲን የትምህርት በመደገፍና በሌሎችም መስኮች ለህረተሰቡ ድጋፍ የሚያደርግ ኩባንያ ነው፡፡
እንግዲህ የስጋ እና ወተት ከብት ለማድለብ፣ የወተት ላሞችን ለማርባት፣ የዶሮ እና ተዋጽኦ ምርቶችን ለማቅብ ሀሳብ እና ስራ እንጅ ወንዝና ደመና ሜዳና ሸለቆ አይወስነውም፣ በርሀ ወይም ደጋ፣ ቆላ ወይም ቀዝቃዛ መሆንም አይወስነውም፡፡
