
የሙዝ የጤና ጥቅሞችና አስገራሚ እውነቶች
ሙዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥር አንድ የፍራፍሬ አይነት የሚል ደረጃ እንዳለው በርካታ የስነ ምግብና የዘርፉ ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡
ሙዝ ከ150 በላይ በሆኑ ሀገራት የሚመረት እጅግ ተወዳጅ የፍራፍሬ አይነት ሲሆን ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ ግን ቀዳሚነቱን የሚይዙት እንደ ህንድ፣ ቻይና፣ ብራዚልና ኢንዶኔዥያ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ናይጀሪያ፣ አንጎላ እና ታንዛኒያ በአፍሪካ በቀዳነት ከሚጠቀሱ ሙዝ አምራች ሀገራት ከፊት የሚሰለፉ ሲሆን ጎረቤት ሀገር ሶማሊያም ከፍተኛ ሙዝ ከሚያርቱ ሀገራት አንዷ ነች፡፡
ሙዝ በበርካታ ዓይነት በመሰራት ከምግብነቱ ባሻገር ወደ ፋብሪካ በመግባትም ለበርካታ የፋብሪካ ውጤቶች እንደ ግብዓት የሚያለግል የፍራፍሬ አይነት ነው፡፡ የሙዝ በተለይም ልጣጩ እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ሲሆን ወደ ፋብሪካዎች በመግባት ለግብዓትነት የሚያለግለውም ይሔው አካሉ ነው፡፡
ለቅባት፣ ለምግብ ማቀነባበር፣ ለመጠጥ፣ ለጨርቃጨርቅ፣ ለኃይል ማመንጫ፣ ለወረቀት ምርት፣ ለባዮ ቴለክኖሎጂ ምርቶች፣ ለግብርና ስራዎችና ለሌሎችም ግብዓት ሆኖ እንደሚያገለግል ይታመናል፡፡
ሙዝ ከህጻን እስከ አዋቂ እጅግ ተወዳጅ ሲሆን ሜዲካል ኒውስ ቱዴይ የተሰኘ የህክምና ጉዳዮችን የሚያሰራጨው የመረጃ አውታር እንዳሰፈረው በርካታ የጤና ጥቅሞች ያሉት ሲሆን አስጊ የጤና ጉዳዮችም አሉበት፡፡

ይህ ፍራፍሬ የልብ ጤንነትን በመጠበቅ፣ በካንሰር የመያዝ እድልን በማስወገድ፣ የደም ግፊትን በማስተካከል. የሰዎችን ቀልብና ሁኔታ በማስተካከል በቀሚዳነት ሲጠቀስ በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ጠንቅ የሚሆንባቸውም ሁኔታዎች እንዳሉ ጽፏል፡፡ ካሉት የጤና ጥቅሞች መካከል፡
- ከደም ግፊት ጋር በተያያዘ
የአሜሪካው የልብ ማህበር ሰዎች ጨው የመጠቀም ልምዳቸውን እንዲቀንሱ፣ ሶዲየም አብዝተው እንዳይመገቡ በሌላ በኩል ግን ፖታሲየም ያላቸውን ምግቦች እንዲያዘወትሩ ያሳስባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፖታሲየም የደም ግፊትን በማስተካከል የልብ ደም ዝውውር ችግርን እንደሚያስተካከል የህክምና ውጤቶች ያሳያሉ፡፡
የማህበሩ መረጃ እንደሚጠቁመውም ሙዝ የሚመገቡ ሰዎች በቀን እስከ 9 በመቶ የፖታሲየም ፍላጎታቸውን እንደሚያሟሉ ያትታል፡፡
- አስም
እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 የተካሄደ ጥናት እንደሚያረጋግጠው ሙዝ መመገብ በተለይም ከአተነፋፈስ ጋር በተያያዘ ህጻናት በአስም የመጠቃት እድላቸውን ይቀንሰዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መዙ በውስጡ ፖታሲየም እና አንቲ ኦክሲዳንት የተሰኙ ኬሚካሎችን በመያዙ ነውና ይላል፡፡
- ካንሰር
በሙዝ ውስጥ የሚገኘው ለክቲን የተሰኘው ፕሮቲን የደም ካንሰር ሊያመጡ የሚችሉ ሴሎች እንዳያድጉ በማድረግ በከፍተኛ መጠን ይከላከላል፡፡
ሌክቲን የተሰኙት ውህዶች በሰውነት ውስጥ ያሉ ቅንጣቶች በማስወገድ ለካንሰር የመጋለጥ እድልን በከፍተኛ ሁኔታ ያስወግዳሉ፡፡ ሙዝ እና የብርቱካን ጭማቂ የሚመገቡ ህጻናት በደም ካንሰር የመጠቃት እድላቸው ትንሽ እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ምክንያቱ ደግሞ ቫይታሚን ሲ በመኖሩ ጸረ ወክሳጅ ውህዶች በብዛት እንዲገኙ ስለሚያደርግ ነው፡፡
- የልብ ጤንነት
ሙዝ በውስጡ ፋይበር፣ ፖታሲየም፣ ፎሌት እና እንደ ቫይታሚን ሲ ያሉ ውህዶችን የያዘ በመሆኑ ለልብ ጤና መጠበቅ አይነተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ከ7 ዓመታት በፊት የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ በምግባቸው ውስጥ ከፍተኛ የፋይበር መጠን ያላቸውን ምግቦች የሚመገቡ ሰዎች ዝቅተኛ ፋይበር ከሚመገቡት የልብ የደም ዝውውር ስርዓታቸው የተስተካከለ እንደሆነ አትቷል፡፡ እነዚህ ሰዎች በኮሊስትሮል የመጠቃት እድላቸውም አነስተኛ ስለመሆኑ መረጃው አካቷል፡፡
- የስኳር ህመም
የአሜሪካው የስኳር ህሙማን ማህበር ባወጣው መረጃ ሙዝና ፋይበር ያላቸውን ፍራፍሬዎች አብዝቶ መመገብ የደም ስኳርን ዝቅ በማድረግ እጅግ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
ይህ አመጋገብ የመያዝ እድልን ከመቀነሱ ባሻገር በበሽታው የተጠቁ ሰዎችንም የስኳር መጠናቸውን በመቀነስ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
- የምግብ መፈጨትን በማስተካከል
ሙዝ በውስጡ ውሃ እና ፋይበር ያለው በመሆኑ የምግብ እንሽርሽሪት እንዲስካከል በማድረግ ትልቅ ሚና ይቻወታል፡፡ አንድ መካከለኛ ሙዝ መመገብ አንድ ሰው በቀን ሊያገኘው የሚገባውን 10 በመቶ የፋይበር ፍላጎት ያሳካለታል ማለት ነው፡፡
እንደ ተቅማጥ ያሉ ችግሮች ፖታሲየም፣ ውሃ እና ኤሌክትሮላይት እንዲወገድ ስለሚያድረግ ሙዝ መመገብ ችግሩን በማስተካከል ረገድ አይነተኛ መፍትሄ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከፍተኛ ፋይበር ያላቸው ምግቦች የሆድ እብጠት አልያም ቁርጠት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆን መፍትሄው ደግሞ ሙዝ መመገብ ስለመሆኑ ጥናቶች ስማሳየታቸው ሜዲካል ኒውስ ቱዴይ ድረ ገጽ ያስነብባል፡፡
- የማስታዎስ ችሎታን መጨመርና ስሜትን/ቀልብነ ማስተካከል
ሙዝ ትራይቶፋን የተሰኘ አሚኖ አሲድ በውስጡ የያዘ በመሆኑ የሰዎችን የማስታወስ ችሎታ ከፍ በማድረግ እንዲሁም ቀልባቸውን በማስተካከል ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡
ሙዝ በዋናነት ባለው የፖታሲየም ንጥረ ነገር ለጤና እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነው፡፡ አንድ መካከለኛ ሙዝ በውስጡ 422 ሚሊግራም ፖታሲየም አለው፡፡ የፖታሲየም መኖር ደግሞ ለልብ ጤና፣ ለኩላሊት ጤንነት እንዲሁም ደም ግፊትን ለመቆጣጠርና የልብ ምትን በማስተካከልም ላቅ ያለ የጤና ጠቀሜታ አለው፡፡
በአጣቃላይ ሙዝ በውስጡ ካርቦሃይድሬት፣ ፋይበር፣ ፕሮቲን፣ ማግኒዚየም፣ ፎስፎረስ፣ ፖታሲየም. ሴሌኒየም፣ ኮሊን፣ ቫይታሚን ሲ፣ ፎሌት፣ ቤታ ካሮቲን እንዲሁም አልፋ ካሮቲን እንደያዘ የጤና መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሌላ በኩል የሰውነት ክብደትን እና አካላዊ ቁመናን በማስተካከልም ሙዝ ጠቃሚ መሆኑን የጤና ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከፍተኛ ፋይበር ዝቅተኛ ክብደት እንዲኖር ስለሚያደርግ፣ ሙዝ ደግሞ ከፍተኛ ፋይበር ያለው ፍራፍሬ በመሆኑ ሙዝን መመገብ ክብደትን ለመቀነስ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሜዲካል ኒውስ ቱዴይ ባሰፈረው መረጃ መሰረት በቀን የምንወስደውን የፋይበር መጠን በ14 ግራም ብንጨምር በአራት ወራት ውስጥ 4 ነጥብ 4 ፓውንድ ክብደት መቀነስ ይቻላል፡፡
በአንድ መካከለኛ ሙዝ ውስጥ 32 ሚሊግራም ማግኒዚየም ያለው በመሆኑ እሱን መመገብ በቀን ከሚያስፈልገው የማግኒዚየም መጠን 8 በመቶውን አገኘን ማለት ነው፡፡
ላኣካል ብቃት እንቅስቃሴም ሙዝ መመገብ ይመከራል፤ ከእንቅስቃሴ በፊትም ሆነ በኋላ ሙዝን መመገብ ኃይል ሰጭ ምግቦችን እንደመውሰድ ነው፡፡
ከ7 እስ 8 ኢንች በሚሆን መካከለኛ ሙሙ ውስጥ 105 ኪሎ ካሎሪ፣ 422 ሚሊግራም ፖታሲየም እንዲሁም 26 ሚሊግራም ፎስፎረስና 0 ነጥብ 31 ሚሊግራም ብረት እንዳለው ይታመናል፡፡
ይሁን እንጅ ሁልጊዜ ሙዝ መመገብ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፤ ምክንያቱ ደግሞ ተያያዥ የጤና ችግሮች ስለሚኖሩ ነው፡፡ ሙዝ በብዛት መመገብ የማይመከርባቸው ሁኔታዎችም
- በኩላሊት ህመም ምክንያት እንደ ቤታ ብሎከርስ የሉ መደ.ሃኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች ሙዝ አብዝተው መመገብ እንደሌለባቸው የጤና ባለሙያዎች የስረዳሉ፡፡ ይህ የጤና ድረ ገጽም መድሀኒቱ የፖታሲየም መጠንን ስለሚጨምር የሙሙ በብዛት መመገብ ፖታሲየምን ከሚፈለገው በላይ ከፍ በማድረግ ሌላ የጤና እክል እንዳያስከትል በመስጋት ነው፡፡
- አለርጂ ያለባቸው ሰዎች ሙዝን መመገብ የሚጠበቅባቸው በህክምና በሚሰጥ አስተያየት መሰረት መሆን አለበት፡፡ የሚያሳክካቸው ወይም የእብጠት ምልክትና የአተነፋፈስ ችግር ያለባቸው ሰዎች የህክምና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳስበው የጤና መረጃው ሙዝን ከመመገብ እንዲታቀቡም ያስገነዝባል፡፡
- ራስ ምታት- ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ሙዝን መመገብ እንደሌለባቸው ይመከራል፡፡ ምክንያቱም የማባባስ እድሉ ከፍተኛ ስለሆነ ነው፡፡
ስለሆነም በተመጣጠነ መልኩ ሙዝ መመገብ ለጤና አስፈላጊ መሆኑን የሜዲካል ቱዴይ መረጃ የሚያሳይ ሲሆን ኢትዮጵያን ቢዝነስ ለአሁኑ ከሙዝ ጠቀሜታ ጋር በተያያዘ ያጠናቀርነው ይህንን ይመስላል፤ ሰብስክራይብ፣ ላይክ እና ሼር ማድረግ እንዳትረሱ፡፡ በሌላ ርዕስ እንመጣለን ጠብቁን፤ ሰላም!
