
የጎንደር ማተሚያ ድርጅት በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን ህንጻ ሲያስመርቅ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉንም አክብሯል፡፡
የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ መስፍን እንደተናገሩት፤ ማተሚያ ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት የህትመት ጥራትና ተወዳዳሪነቱን በማሳደግ ፈር ቀዳጅ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
ማተሚያ ድርጅቱ በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው አዲሱ ህንጻ ለህትመት ስራዎች፣ለምርት ማከማቻና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ክፍሎች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡

በ215 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ወደ ህትመት ኢንዱስትሪው የተቀላቀለው ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱን ጠቅሰው፤ 32 ዘመናዊ የህትመት ማሽኖች እንዳሉትም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ለ173 ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በህትመት ኢንዱስትሪው ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢዜአ
