ጤፍ እና በቆሎን በዘመናዊ መንገድ ለመውቃት- ኤልያስ ኢንጂነሪንግ

Spread the love

ማንኛውንም አዝርዕት በዘመናዊ መንገድ ለመውቃት- ኤልያስ ኢንጂነሪንግ

ኤልያስ በቀለ የማሽነሪ ዲዛይነር ሲሆን የኤልያስ በቀለና ጓደኞቻቸው አጠቃላይ ኢንጂነሪንግ እና ብረታብረት ስራ ሽርክና ማኅበር ወይም በአጭሩ የኤልያስ ኢንጂነሪንግ ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡

ድርጅቱ በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ሜካናይዜሽን የበለጠ ለማዘመን የበርካታ ሰብሎችን መውቂያ ቴክኖሎጂ በማምረት ለአርሶ አደሩ ትልቅ የለውጥ አጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ኤልያስ በቀለ ገለጻ ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ከ6 በላይ የመውቂያና ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በማምረት ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ላይ ሲሆን ማንኛውንም ሀሳብ ይዞ ለሚመጣ ግለሰብ እንደ ሀሳቡ ዲዛይኑን በመስራት ማሽነሪውን ማምረት ይችላሉ፡፡

በዋናነት በበቆሎ፣ በጤፍ፣ በአኩሪ አተር፣ በዳጉሳ ፣ በስንዴ እና በመሳሰሉት ምርቶች ዙሪያ ማሽነሪዎችን የሚያመርተው ኤልያስ ኢንጂነሪንግ በሌሎችም የግብርና ምርቶች ዙሪያ ማሽነሪዎችን እንደሚያቀርብ ለኢትዮጵያን ቢዝነስ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ዘመናዊ የእህል ጎተራ እና የትራክተር ጋሪዎችን በማምረት የግብርናው አጋር በመሆን እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የማሽነሪዎቹ በሀገር ውስጥ መመረት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የሚገልጹት አቶ ኤልያስ በቀለ የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት፣ የምርት ብክነትን በከፍተኛ ደረጃ በማዳን፣ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል በመፍጠርና ጊዜ እና ጉልበትን በመቆጠብም ትልቅ ሚና እንደሚጫዎት አብራርተዋል፡፡

በባህላዊ መንገድ በበሬ በማበራየት ቀናትን የሚወስደውን የጤፍና በቆሎ የመውቃት ሂደትን በማሳጠር ሳይባክንና ጊዜ ሳይወስድ ለምርትን ወደ ጎተራ ለማስጀገባት የሚሰሩት ማሽን አይነተኛ መፍትሄ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

አንዱ በትራክተር ጉልበት የሚሰራ የበቆሎ መፈልፈያ ብቻ በቀን እስከ 800 ኩንታል መፈልፈል እንደሚችም ገልጸው ትራክተሮች ከእርሻው ጎን ለጎን በውቂያ ወቅትም እንዲያገለግሉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ሶስት አይነት የበቆሎ የመፈልፈያ ማሽነሪዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ኤልያስ በቀለ እስከ 1 ዓመት የሚደርስ ዋስትና እንደሚሰጡ ገልጸው ከዚህ በፊት በባህላዊ መንገድ የሚመረተው ምርት የመሰባበር፣ የመጎዳት እና የመባከን እድሉ ሰፊ እንደነበር አውስተዋል፡፡

አብዛኛው አካባቢ ጤፍ እንደሚመረት የገለጹት አቶ ኤልያስ በአሁኑ ወቅት ጤፍ ላይ ውጤታማ ማሽኖችን እያሰራጩ መሆናቸውን ተናግረው ባለፈው አመት ብቻ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመዋዋል ከ30 በላይ የውቂያ ማሽነሪዎችን ስለማሰራጨታቸው አብራርተዋል፡፡

ጤፍ ብቻ ሳይሆን ዳጉሳንም በመውቃት ውጤታማ የሆነ ማሽን መስራታቸውን ገልጸው የመለዋወጫ ወንፊቶችን እና የተለያዩ ሞተሮችን በመግጠም ብቻ አንዱ ማሽን ከ6 በላይ አዝርእቶችን መውቃት እንዲችል ተደርጎ ስለመሰራቱም ጠቁመዋል፡፡  

በትራክተር ተጠቅሞ ጤፍ መውቃት የሚችል ማሽን ወደ ስራ ስለመግባቱ የተናገሩት አቶ ኤልያስ ከግዥ ጋር በተያያዘ በቀጥታም ሆነ እንደ ኦሮሚያ ፋይናንስ እና ዋልያ ፋይናንስ ባሉ የብድር ቁጠባ ተቋማት በብድር ወይም በባንኮች በኩል በማስተሳሰር እያሰራጨን ነው ብለዋል፡፡

በተመጣጣኝ ዋጋ ከአንድ ዓመት ዋስትና ጋር የሚቀርቡ እንደየሞተር አቅማቸው በተለያዬ መጠን የጤፍ መውቂያ ማሽኖች ከ220 እስከ 260 ሺ ብር እንደሚሸጡ ገልጸው በትራክተር የሚሰሩ ደግሞ ከ320 እስከ 350 ሺ ብር ድረስ እንደሚሸጡም አብራርተዋል፡፡

የበቆሎ 3 ዓይነት መፈልፈያ መኖሩን ያነሱት ስራ አስኪያጁ አነስተኛ የተሸለቀቀ በቆሎ መውቃት የሚችለው ተንቀሳቃሽ ባለጎማ የሞተር ጉልበትና እስከ 40 ኩንታል በሰዓት የሚፈለፍለው ከ185 እስከ 200 ሺ ብር ድረስ ይሸጣል ነው ያሉት፡፡

በትራክተር የሚሰራው በሰዓት ከ80 እስከ 100 ኩንታል የሚሰራው በተለምዶ ባኮ ሞዴል የሚባል ሲሆን ከ200 እስከ 220 ሺ ብር ድረስ ለተጠቃሚዎች እየተሸጠ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ትልቁ የበቆሎ፣ አኩሪ አተርና ሌሎችን የአተር ዝርያዎች መውቃት የሚችለው ያልተሸለቀቀ በቆሎ መውቃት የሚችል ሲሆን በሰዓት ከ60 እስከ 80 ኩንታል ያመርታል፡፡

ኢንቨስተሮች በብዛት እንደሚጠቀሙትና እንደ ጋምቤላ ክልል እና ነቀምት ባሉ አካባቢዎች በብዛት በስራ ላይ ሲሆን ባለ አራት ጎማ ተሸከርካሪ ነው ተብሏል፡፡

ማሽነሪዎችን ለማምረት የግብዓት ማግኘትን ጨምሮ ብቁ ሰው ኃይል አለመኖሩን አንስተው ድርጅቱ ባለሙያዎችን ከቀጠረ በኋላ የስራ ላይ ስልጠና እየሰጡ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢኮኖሚው ላይ የምርት እና ስራ እሴት ሰንሰለት በመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያብራሩት አቶ ኤልያስ ማሽነሪው ያለው አርሶ አደር ከራሱ ባሻገር ለሌሎች አርሶ አደሮች በማከራየትም ተጨማሪ ስራ እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ሌሎች የጎረቤት ሀገራት ማሽነሪዎችን በመላክ ለመስራት እየተጉ መሆኑን የገለጹት ስራ አስኪያጁ ሰፊ ገበያ እንዳለም ተረድተናልም ብለዋል፡፡

ከማሽነሪ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለአርሶ አደሩ ስልጠና በመስጠት እንዲጠቀሙ እያደረጉ መሆናቸውን አንስተው ለሁሉም ምርቶች መውቂያነት የሚያገለግል (Multi Crop Thresher Machine) እና የእንስሳት መኖ መከትከቻ እና ማዘጋጃ ማሽነሪዎችንም እያመረቱ ስለመሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ማንኛውም አርሶ አደርም ሆነ ተቋም ማሽነሪዎችን መግዛትም ሆነ ማሰራት ቢፈልግ ድርጅቱ ማሽነሪውን መስራትና ወደ ሚፈለገው ቦታ ማድረስ እንደሚችልም ስራ አስኪያጁ ለኢትዮጵያን ቢዝነስ ተናግረዋል፡፡

ኤልያስ ኢንጂነሪንግ በሰራቸው የቴክኖሎጂ ስራዎች የኢፊዴሪ አእምሯዊ ንብረትን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና ውጭ ተቋማት የእውቅና ምስክር ወረቀት እንደተበረከተለት ለማወቅ ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *