ዘመን ኢንሹራንስ ኩባንያ ትርፉን ከ3 እጥፍ በላይ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡

Spread the love

ዘመን ኢንሹራንስ ኩባንያ ዓመታዊ ትርፉን ከ3 እጥፍ በላይ ማሳደጉን አስታወቀ፡፡

ኩባንያው የ2016 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ለሪፖርተር እንዳሳወቀው፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 181.3 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡

ከታክስ በኋላ ያገኘው የትርፍ መጠን 151.3 ሚሊዮን ብር መሆኑን የኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ከታክስ በፊትም ሆነ በኋላ ያገኘው ትርፍ ኩባንያው ወደ ሥራ ከገባበት አራት ዓመት ወዲህ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ ዘመን ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አግኝቶት የነበረው ትርፍ 45.9 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ የ545.3 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ይህ የዓረቦን ዓረቦን ቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ67.5 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ የዓረቦን ምጣኔውን በዚህ ደረጃ ማሳደግ መቻሉ፣ የዘመን ኢንሹራንስ ራሱን የገበያ ድርሻ ማሳደግ አስችሏል፡፡፡ ኩባንያው የቀደመው ዓመት ገበያ ድርሻው በ18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የነበረው ሲሆን፣ በተያዘው ሒሳብ ዓመት ግን ደረጃዎችን በማሻሻል ወደ 14ኛ  አሳድጓል፡፡

ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘም ኩባንያው በ2016 የሒሳብ ዓመት፣ በአጠቃላይ 103.3 ሚሊዮን ብር ጠቅላላ የካሳ ክፍያ የፈጸመ ሲሆን፣ ለካሳ ከተከፈለው ውስጥ ለተሽከርካሪ ዋስትና የተከፈለው የካሳ መጠን ትልቁን ድርሻ የያዘ ነው፡፡

 ኩባንያው ከመድን ውል ሥራ (Underwriting Result) የ166.2 ሚሊዮን ብር ውጤት ያገኘ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ በበጀት ዓመቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ 74 በመቶ  የትርፍ ድርሻ (Earning Per Share)  ለባለአክስዮኖች አዳስገኘም ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ዘመን ኢንሹራንስ ከተመሠረተ 4 ዓመት የሞላው ሲሆን፣ ጠቅላላ ሀብቱን ወደ 961.5 ሚሊዮን ብር አድርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉም ወደ 234.2 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡ በመላ የአገሪቱ በከፈታቸው ቅርንጫፎች 30 ደርሰዋል፡፡

መረጃው፡ የሪፖርተር ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *