አሮጌ ወረቀትን ወደ እቃ የሚቀይረው Ande Mama

Spread the love

አሮጌ ወረቀትን ወደ እቃ በመቀየር ወደ ዘላቂ ውበት የሚቀይረው Ande Mama የተሰኘው ድርጅት፡፡  

አንዴ ማማ የማያስፈልጉ የወዳደቁ የወረቀት ምርቶችን እንደገና መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡ ተቋሙ የማያገለግሉና ሚወገዱ የጋዜጣ፣ የመጽሔት እና ሌሎች የህትመት ውጤቶችን በማሰባሰብ እንደገና ጥቅም ላይ የሚያውል ሀገር በቀል ተቋም ነው፡፡  

ሐና ግርማ የአንዴ ማማ የማርኬቲንግ ባለሙያ ነች፡፡ ሐና እንደምትለው አንድን ወርቀት እስከ 7 ጊዜ እንደገና መልሶ መጠቀም ይቻላል፡፡ በአንዴ ማማ የወረቀት ውጤት እቃዎችና ጌጣጌጦች ማምረቻ ጋዜጦችንና ወረቀቶችን በመሰብሰብ በተለያዩ የእቃዎች ዲዛይን በመስራት ለስጦታ፣ ለእቃ ማስቀመጫ፣ ለጌጣጌጥ፣ ለከረጢት እንዲሁም ለቤትና ቢሮ ማስዋቢያ የሚያገለግሉ እቃዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ሀና ትናገራለች፡፡

የስጦታ እቃዎች፣ መያዣዎችና የማስዋቢያ ቁሳቁሶች በብዛት ከውጭ ይገባሉ የምትለው የማርኬቲንግ ባለሙያዋ እነዚህን ምርቶች በወረቀት ውጤቶች መተካትና ባህላዊ እሴታቸውን የጠበቁ ቁሳቁሶችን ማምረት ነው ትላለች፡፡

ለመንግስተና የግል ተቋማት የተለያዩ ዲዛይኖችን፣ የጠረጴዛ እቃዎችንና የመሳሰሉትን ቁሳቁሶችን በትእዛዝ እየሰራን ነው የምትለው ሃና በተቋማት መለያ ሎጎ በመስራት የውበት ስራዎችንም እየሰራን ነው ትላለች፡፡

ወረቀቶችን ከተቋማት በመረከብና በስጦታ በመቀበል እያመረትን እንገኛለን የምትለው ባለሙያዋ ከውጭ ከሚገቡት ምርቶች ዋጋ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ መሆኑን በመጠቆም የሚወገዱ ምርቶችን በመጠቀም የሚሰራ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑን ለኢትዮጵያን ቢዝስ ጠቁማለች፡፡

የውስኪ መያዣ እቃዎች፣ የእስክብሪቶና የጽሕፈት መሳሪያ ቅርጫቶች፣ ልዩ ልዩ የግድግዳ ጌጦች፣ የጌጣጌጥ ማስቀመጫ ሙዳዮች፣ የስጦታ እቃዎች፣ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እያመረተም ለተቋማት ያቀርባል፡፡

የወረቀት ቁሰቁሶቹ ከውኃ የሚከላከሉ (Waterproof) ምርቶች በመሆናቸው በየትኛውም ቦታ እና ሁኔታ ውኃ ቢነካቸው የማይበላሹና ወድቀው የማይሰበሩ በመሆናቸው ረጅም ጊዜ የሚቆዩ መሆናቸውም ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ሐና ትገልጻለች፡፡

አንዴ ማማ እናቶችን በማሰባሰብና በማሰልጠን ራሳቸውን በገቢ እንዲደጉሙ እያደረገ መሆኑን የተናገረችው የማርኬቲንግ ባለሙያዋ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የተደራጁ እናቶችን በማገዝና በማሰልጠን ላይ መሆኑን አብራርታለች፡፡

ተቋሙ እናቶችን የሚደጉምና የሚባክነውን የወረቀት ምርት መልሶ በመጠቀም ለጽዳትና ለአካባቢ ብክለት መከላከል አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ተቋማት የሚወገዱ የጋዜጣና የወረቀት ምርቶች ካሏቸው እንዲሰጧቸውም ጠይቃለች፡፡

አንዴ ማማ የሚለው ስያሜ ህጻናት እናቶቻቸውን ማማ አንዴ እንዲህ ላድርግ አንዴ እንደዚያ ….ወዘተ እያሉ እናቶቻቸውን… አንዴ…አንዴ….. እያሉ በተደጋጋሚ  ከሚያደርጉት ጥሪ የመጣ መሆኑንም ለመረዳት ችለናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *