ሙዳይ፣ አገልግል፣ ማኛ፣ ሌማትና ማዕድ- የአማሔ ምጣድ ስሞች

Spread the love

ሙዳይ፣ አገልግል፣ ማኛ፣ ሌማትና ማዕድ- የአማሔ ምጣድ ስሞች

የምግብ ማብሰያ ቴክኖሎጂዎች በተለይም የምጣድ እና የምድጃ ቴክኖሎጂዎች የተሻሻለ የመጣ ሲሆን እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የኤሌክትሪክ ፍጆታቸው ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበትና ለምግብ ተስማሚ ከሆኑ መሳሪያዎች መመረት እንደሚገባቸው የስነ ምግብ ባለሙያዎች ያነሳሉ፡፡

አልሙኒየም፣ ካስት ብረት እንዲሁም የሴራሚክ፣ የሸክላ ምርቶችና የመሳሰሉት ቁሳቁሶች ከሌሎች መስሪያ ግብዓቶች ጋር ሆነው ለምግብ መስሪያ ቁሳቁስነት የሚመረጡ ሲሆን በተለይ እንደ ምጣድና ምድጃ ያሉ መሳሪያዎች በመጠንም ሆነ በኤሌክትሪክ ፍጆታቸው እየተሻሻሉ መጥተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጥራት ማረጋገጫ እንደሚያስፈልጋቸው ዘርፉ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

አቶ ዮሐንስ አየለ የምጣድና ምድጃ አምራች የሆነው የአማሔ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት 12 ዓይነት የምጣድ አይነቶችን ለ24 ሰዓት እያመረቱ መሆናቸውን ገልጸው ደረጃቸው የተሻሻሉ ምርቶችን የአእምሯዊ ንብረት እስከማግኘት መድረሳቸውን ለኢትዮጲያንቢዝነስኢንፎ ገልጸዋል፡፡

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ ለምግብ ተስማሚ ከሆነ አልሙኒየም የሚሰሩት የምጣድ ምርቶች ኃይል ቆጣቢ ሆነው ስለመሰራታቸው ነው የገለጹት፡፡ ምርቶች በቂ መለዋወጫ እና የጥገና እድል ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ዮሐንስ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ከጥሬ እቃ ጀምሮ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ በመሆናቸው ትልቅ እሴት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የምጣድና የምድጃ ምርቶች ከጥራትና ከብቃት ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸው ተቋማት መቆጣጠርና በአግባቡ ክትትል እንደሚያስፈልገው በማንሳት ዋጋውም የተጠቃሚውን አቅም ያገናዘበ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡት የምድጃ ምርቶች የጥራት ችግር ቢያጋጥቸውና ለጥገና ምቹ ባለመሆናቸው ችግር እንዳለባቸው በማንሳት ከተጠቃሚው ፍላጎት አንጻር ተጠንተው ባለመመረታቸው አመቺነታቸው አጠያያቂ ስለመሆናቸው ያነሳሉ፡፡

አማሄ የሚያመርታቸው ምድጃዎች ከውጭ የሚገቡትን ተክተው ስለመመረታቸው ጠቅሰው ይህ ደግሞ የራስን ሀብት ለራስ መጠቀም በመሆኑ ተመራጭነት እንዳለው አንስተዋል፡፡

የምጣድ ምርቶች ከሸክላ ውጭ የሚሰሩ አይደሉም የሚሉት አቶ ዮሐንስ በአሁኑ ወቅት በተለጣፊ፣ በተጣጣፊ እና በተንቀሳቃሽ እንደ ነዋሪው ፍላጎት ተመርተው በሱፐር ማርኬቶች እንደማንኛውም እቃ በተመጣጣኝ ዋጋ በሽያጭ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ሀገርኛ ስያሜ ያላቸው ምጣዶች በመመረት ላይ ናቸው ያሉት ስራ አስኪያጁ አቶ ዮሐንስ ሙዳይ፣ ማዕድ፣ ሌማት፣ አገልግል፣ ማኛ ወዘተ እተባሉ የሚጠሩ ሲሆን እንደ ስያሜያቸው ቅርጻቸውም የተለያዩ ሲሆን ከ7 ሺ ብር ጀምሮ በሽያጭ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡

ሙዳይ የተሰኘው ምጣድ ጠረጴዛ ላይ የሚቀመጥ ሲሆን አገልግል ደግሞ ግድግዳ ላይ የሚቀመጥ እንዲሁም ሌሎቹም በተመሳሳይ እንደ ስያሜያቸው በተለያየ ቅርጽ ስለመሰራታቸው አብራርተውልናል፡፡

በሁለቱም የምርት ዓይነቶች ከ7 በላይ በሚሆኑ መሐንዲሶች በየጊዜው የማሻሻያ ስራዎች ይሰራሉ ያሉት አቶ ዮሀንስ የምድጃ ምርቶች ከ1 ሺ ብር ጀምሮ ለሽያጭ መቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

2 Comments

  1. እንደሰማነው ከሆነ በጣም ጥሩ መረጃ ነው የሰጣችሁን መተን ደሞ ምርታችሁን ለመግዛት ቦታችሁን ብትነግሩን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *