ልባሽ ጨርቅ በቢሊየን ዶላር የሚንቀሳቀስበት የዓለም ቢዝነስ ዘርፍ

Spread the love

ልባሽ ጨርቅ በቢሊየን ዶላር የሚንቀሳቀስበት የዓለም ቢዝነስ ዘርፍ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ96 የንግድ ሸቀጦች መካከል ልባሽ ጨርቅ 44ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ መረጃዎች አሳይዋል፡፡ 

ኣሜሪካ፣ ቻይና፣ ህንድ እና ፓኪስታን እንዲሁም ጀርመን እና ተርኪየ ልባሽ ጨርቆችንና አልባሳትን ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ ቀዳ ሀገራት ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡

ባለፈው ጥቅምት/2024 በወጣው መረጃ ቻይና ብቻ ከ313 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ሰልቫጅ አልባሳትን ወደ ሌሎች ሀገራት ስትልክ ይህ ቁጥር ግን በዩናይትድ ስቴትስ ከ351 ቢሊየን ዶላር በላይ ስለመሆኑ የስታቲስታ መረጃ ያሳያል፡፡ አውስትራሊያ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ ስለመያዟ ነው የተገለጸው፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ የልባሽ ጨርቆች ጠቅላላ የገበያ ዋጋ 197 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ እንደ ኬንያ፣ ጓቴማላ እና ፓኪስታን ያሉ ሀገራት ደግሞ በቀዳሚ የእነዚህ አልባሳት መዳረሻነት ይጠቀሳሉ፡፡

የሴቶች፣ የወንዶች እና የህጻናት በሚል የሚከፈሉት የልባሽ ጨርቆች ገበያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቢቢነስ የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ሀገራት ልባሽ ጨርቆችን አልገዛም በሚሉ ሀገራት ላይ ከአጎዋ እድል እስከ መከልከል የደረሰ እርምጃ የምትወስደው፡፡

አንድ ልባሽ ጨርቅ እንደ ሰልቫጅ ሆኖ ለመሸጥ ከሶስት እስከ አምስት አመታት ይለበሳሉ፡፡ እነዚህ አልባሳት በአንድ ሰው በነዚህ ዓመታት ለተከታታይ ወይም አልፎ አልፎ ከተለበሱ በኋላ እንደ ገና በቦንዳ ታሽገው ወደ ሌሎች ሀገራት ይላካሉ እንደገና በሌሎች ዜጎች ይለበሳሉ፡፡ እነዚህ አልባሳት እንደገና እንደ አልባሳቱ አይነት እስከ 6 ዓመታት ሊለበሱ እንደሚችሉ ነው ዘርፉ ላይ የሚሰሩ አካላት የሚናገሩት፡፡

ከጃኬት እና ጅንስ ሱሪዎች እስከ ቲ ሸርት እና እስከ ውስጥ ልብስ እና ፓንት ድረስ አልባሳቱ በመርከብ ተጓጉዘው ወደ ሶስተኛው አለም አፍሪካ እና እስያ እንዲሁም የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ይደርሳሉ፡፡

የአልባሳት ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ ልብስ እስ 2 ዓመት ጊዜ እንደሚለበስ ይገልጻሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ግን ከዚህም በላይ ለረጅም ዓመታት እንደሚለበስ ነው የሚገልጹት፡፡

የተለበሱ አልባሳት ወደ ሌሎች የበጎ አድራጎት ተቋማት ከሚሄዱ እንዲሁም ወደ ቆሻሻ ማስወገጃ ጣቢያዎችና ወደ አፈር ማልበሻ ማዕከላት ከሚጓጓዙ እንደ ገና መጠቀም ወደሚቻልበት አማራጭ መሄድ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

ወደ ሌሎች ሀገራት በታላላቅ መርከቦች ተጓጉዘው የሚደርሱት አልባሳት ካላቸው ጠቀሜታ ባለፈ ሊይዟቸው የሚችሉ ባክቴሪያዎች በሽታዎችን መጀመሪያ ከለበሰው ሰው እንደ ገና ወደሚለብሰው ሰው በማስተላፍ አሉታዊ ጎናቸው ሰፊ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በአግባቡ ከጸዱና በተገቢው መልኩ ከተደረደሩና ከተጫኑ እንደገና መለበስ መቻላቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚያዩትም በርካቶች ናቸው፡፡

በእንግሊዝ በየሳምንቱ ከ13 ሚሊየን በላይ አልባሳት እንደሚቀበሩ ነው የኦክስፋም መረጃ የሚያሳየው፡፡

በአፍሪካ ልባሽ አልባሳት ንግድ በስዋሂሊ ቋንቋ ሚቱምባ ሲሰኝ ማሸግ ወይም አንድ ላይ መጠቅለል የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ዘርፉ እጅግ የደራ ገበያ ያለበት ሲሆን በርካታ ኩባንያዎችም ከአውሮፓ አሜሪካ እስአ ፍሪካ የጠረፍ ሀገራት ድረስ ያጧጡፉታል፡፡

ኮሃን ቴክስታይል ጆርናል በሚገርም ሁኔታ የአፍሪካ የልባሽ ቸርቅ እድል እና የአውሮፓ ዘላቂ የፋሽን ኢንዱስትሪ በሚል ባሰፈረው ጽሁፍ የልባሽ ሰልቫጅ አልባሳት ወደ አፍሪካ በገፍ መጓጓዝ መግዛት የማይችሉ በአቅማቸው እንዲለብሱ፣ እንዲሁም የተለበሱ አልባሳትን በመሰብሰብ፣ በማጽዳት፣ በመደርደርና መልሶ በመሸጥ ሂደት ባለው ሰንሰለት የስራ እድል ይፈጥራል ይላል፡፡ ቆሻሻን በማስወገድ ረገድም ትልቅ ጥቅም እንዳለው የሚያትተው ይህ ድረ ገጽ በተለይም በመሬት ውስጥ የሚቀበረውን የአልባሳት መጠን በመቀነስ የላቀ ጽዳት ፋይዳ እንዳለው ያብራራል፡፡

ኣፍሪካውያን የፋሽን ተከታይ እንዲሆኑና አምረው እንዲታዪ በማድረግ ካለው ሚና ባሻገር ለበጎ አድራጎትነ ማህበራዊ አገልግሎትም ተመራጭ ነው ሲል ያስነብባል ኮሃን ቴክስታይል ጆርናል፡፡

ይሁን እንጅ ያለውን አሉታዊ ጎንም አብራርቷል፡፡በቀዳነትም የሀገር ውስጥ ልብስ አምራቾችን ከገበያ በማስወጣት ሀገርኛ የዘርፉ አምራቾች እንዳይኖሩ በማድረግ ሁልጊዜ የውጭ ተመልካች እንዲሆን ያደርጋል ይላል፡፡

ባሌላ በኩል አፍሪካውያን እንደገና በእጅ አዙር ቅኝ ተገዥ የሚሆኑበት፣ ጥገኛ የሚያደርግ አንዱ ዘርፍ ነው ሲል በአሉታዊ ጎኑ አስፍሮታል፡፡

የጤና ስጋት በመደቀንም አንዱ የስጋት ዘርፍ ስለመሆኑ የሚያብራራው ድረ ገጹ ቫይረስና ባክቴሪያን በቀላሉ በማሰራጨት ስጋት የሚሆንበት እድሉ ሰፊ በመሆኑ ጠንካራ የጥራትና ስታንዳርድ ቁጥጥር ስረዓት መኖር እንደሚያስፈልግም ነው የገለጸው፡፡

የሀገር ውስጥ አምራቾችን መደገፍ፣ ማበረታታት፣ የትምህርትና ስልጠና ስረታዎችን መስጠት፣ የጥራትና ቁጥጥር ህጎችን ማጥበቅ ለሀገርኛ አምራቾች እደል የሚፈጥር በመሆኑ የልባሽ አልባሳት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚያደርጋቸው ነው፡፡

እንደ ዛጉሚ ያሉት የቻይና ኩባንያዎች ያገለገሉ ልባሽ አልባሳትን እንዲሁም ጫማ እና ቦርሳዎችን በደረጃ በመከፋፈል በመላው ዓለም በጅምላ በመሸጥ ይታወቃሉ፡፡

ከዚህ ባለፈ ከአውሮፓ እና ከሌላው ዓለም በብዛት ወደ አፍሪካ ከፍተኛ መጠን ያለው ሰልቫጅ ልብስ እንደሚያስገቡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በአፍሪካ በተለይም ሰልቫጅ ልብሶች በብዛት በሚገበያዩባቸው እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ እና ኬንያ ባሉ ሀገራት በዝቅተኛ ነዋሪው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ኢኮኖሚ ባላቸው ሰዎች ዘንድም ተመራጭ ሲሆኑ ይስተዋላል ብሏል ኢውሮሞኒተር ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም ባወጣው መረጃ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ማዱኑሳ፣ በናይጀሪያ ኦክሪካ  እንዲሁም በኬንያ ምቱምባ የተሰኘው የልባሽ ጨርቆች ገበያ በኢትዮጵያም በተለምዶ ሰልቫጅ/ሰከንድ ሀንድ እየተባለ ይጠራል፡፡

ሂሰን ግሎባል የተሰኘው እና ልባሽ አልባሳትን ከ60 በላይ ለሚሆኑ ሀገራት የሚያቀርበው የቻይናው ኩባንያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ወደ አፍሪካ፣ የደቡብ ምስራቅ እስያ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከ120 በላይ የአልባሳት አይነቶችን ለሽያጭ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያም በየቀኑ ከ10 ሺ በላይ የልባሽ ጨርቅ ቦንዳ እንደሚገባ ይፋ ሲደረግ ታይዋን፣ እፎይታ እና እንከን በሚል ምድብ ልባሽ አልባሳቱ ወደ ገበያ እንደሚገቡም ተጠቅሷል፡፡

ታይዋን የተሰኘው የአልባሳት ምድብ የተሻለ ጥራት ያለው ሲሆን ከመደበኛው ገበያ በቅናሽ በተለይም በአዲስ አበባ በቦሌ እና ሃያ ሁለት በተባሉት የገበያ ቦታዎች የሚሸጡ ስለመሆናቸው የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾ ማህበር ይገልጣል፡፡

እፎይታ የተባለው ደግሞ በብዛት ከታይላንድ የሚገቡ እና በብዛት መርካቶ አካባቢ ለሽያጭ የሚቀርቡ ሲሆን እንከን የተሰኘው ምድብ ደግሞ መታጠብና እንደገና መሰፋትና መስተካከል የሚያስፈልጋቸው የተበላሹና እንደገና መጠገን የሚስፈልጋቸው ሲሆን አጠና ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚሸጡ ስለመሆናቸው በዘርፉ የተሰራው ጥናት ያሳያል፡፡

ልባሽ አልባሳት ፍትሀዊ ያልሆነ የገበያ ውድድር በመፍጠር፣ የኢንዱስትሪውን አሰራር በማበላሸት፣ ጥራት የሌላቸውን ምርቶች ወደ ተጠቃሚ በማቅረብ እንዲሁም የቅጂና ፈጠራ መብቶችን በመጣስ የአእምሯዊ ንብረቶችን በማባዛትና ፈጠራን ስለሚያኮስስ ተጽእኖው ትልቅ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

ለቆዳ እና ሌሎች በሽታዎች በማጋለጥ ህብረተሰቡን ለሌላ ችግርና ወጭ በማጋለጥ ተጨማሪ እክል የሚፈጥረው የአልባሳት ህገ ወጥ ንግድ መንግስት መሰብሰብ የሚገባውን ገቢ እንዲያጣ በማድረግም እንቅፋት ይፈጥራል፡፡

በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ያለምንም ቀረጥና ተጨማሪ ግብር ከ54 ሚሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶች ወደ ሀገር እንደሚገቡ የተገለጸ ሲሆን እስከ 45 ሚሊየን ዶላር ገቢ እንደሚያሳጣም ይታመናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *