
https://www.youtube.com/@Ethiopianbusiness2024
ጳጉሜን የቁጠባና ብድር የኅብረት ስራ ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ የብድር ጣሪያውን 5 ሚሊየን ብርና የመመለሻ ጊዜውንም 10 ዓመት አደረገ፡፡
ጉባኤው ዶ/ር ጋሻውበዛ አያሌውን የማኅበሩ ምክትል ሰብሳቢ አድርጎ መርጧል፡፡
በ2ኛው ጠቅላላ ጉባኤ የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ መኮንን በፕሮግራሙ ላይ ቁጠባ ገንዘብንም በስርዓት መጠቀም፣ ብክነትን ማስወገድ፣ ጥሪት ማካበት፣ ፍላጎትን ስርዓት ባለው መንገድ ማስተናገድ፣ ከዕለት ፍጆታ ቀንሶ ለወደፊት ማስቀመጥ አርቆ ማሰብ ማለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቁጠባ ገንዘብ ለችግር ጊዜ፣ ለድንገተኛ አደጋዎች መጠባበቂያ፣ ለወጪዎች መሸፈኛ የሚያገለግል ሲሆን ለእቅድ ማስፈፀሚያ እየኖሩ መቆጠብ፣ እየቆጠቡ መበደር ፣የተበደሩትንም በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል ብልህነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በጉባኤው ላይ አሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተወካዮች ያላቸውን ተሞክሮ ለተሳታፊዎች አስረድተው አስፈላጊውን ድጋፍ፣ ሞያዊ እገዛና ስልጠናዎችን እንደሚሰጡና የጳጉሜን ጅማሬም ተስፋ ሰጪ መሆኑን አብራርተዋል

የወጋገን ባንክ ተወካይ በበኩላቸው በዘርፉ ላይ ያላቸውን ልምድ እና ነባራዊ ሁኔታ በማብራራት ከማህበሩ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
ጉባኤው በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይቶ ያጸደቀ ሲሆን የተጓደሉ የስራ አመራር ኮሚቴዎችን ሲያሟላ ዶ/ር ጋሻውበዛ አያሌውን ምክትል ሰብሳቢ እና ዶ/ር ደመቀ ሹምየ፣ ወ/ሮ ገነት እና አቶ ምንይችል ቤዛን የቁጥጥር ኮሚቴ አድርጎ መርጧል፡፡
በውይይቱ የብደር አገልግሎት 3 በመቶ እና የመድን ክፍያ 3 በመቶ እንዲሆንም ውሳኔ ተላልፏል፡፡ የማህበሩ የብድር መጠቂያ ወቅት 6 ወር በተከታታይ ለቆጠበ እንዲሆንም ጉባኤው ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ኅብረት ስራ ጽህፈት ቤት ተወካይ ባለሞያዎችም በማህበሩ ኦዲት ሪፖርት ላይ አስተያየት ሲሰጡ የገንዘብ እጥረትን ለመቅረፍ እንደ አሚጎስ ካሉ ማህበራት ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የኅብረት ስራ ማህበር የሚለው የማህበሩ ስያሜ ጳጉሜን የቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የኅብረት ስራ ማህበር በሚል እንዲስተካከል ተወስኗል፡፡
የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ መኮንን ለማህበሩ መጠናከር ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና የቀረበላቸው ሲሆን ከድርጅታቸው 10 ሚሊየን ብር ብድር እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል፡፡
