
ከ20 ሺ በላይ አሳማዎችን የሚያረባው ባለ 26 ፎቅ ህንጻ የእርባታ ማዕከል
ይህ ህንጻ የቅንጡ ሀገር ቤተ መንግስት ወይም ግዙፍ የገበያ ማዕከል አልያም ፋብሪካ አይለም ይልቁንም በቻይና የሚገኝ ግዙፉ የአሳማ እርባታ እና ማቀነባበሪያ ማዕከል ነው፡፡ ይህ ማዕከል እንግዲህ በሀገሪቱ ሁበይ ግዛት ዝሆንግዚን ካይዌይ ዘመናዊ የአሳማ እርሻ በሚል የሚታወቀው ኢዞ በተሰኘችው ከተማ ዳርቻ የሚገኝ ግዙፉና ያልተለመደ ሰማይጠቀስ የአሳማ እርባታ ጣቢያ ነው፡፡
ይህ ባለ 26 ወለል ህንጻ እጅግ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት እና ማዕከላዊ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ያለው 20 ሺ በላይ አሳማዎች የሚረቡበት ሲሆን በዓመት እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አሳማዎችን በማቀነባበር የሚታወቅ ተቋም ነው፡፡
ከሻንሃይ 500 ማይል ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ማዕከል በ800 ሺ ስኩየር ሜትር ላይ የተንጣለለና የግማሽ ቢሊየን ዶላር መሰረተ ልማት ፈሰስ የተደረገለት ማቀነባበሪያ ስፍራ ነው፡፡
ይህ ማዕከል በዓለም ደረጃ በአንድ ህንጻ ላይ ያለ ትልቅ እርሻ ነው፡፡ የአሳማ ስጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተመራጭ ሲሆን ቻይና የዓለምን ግማሽ የአሳማ ስጋ በመጠቀም ትታወቃለች፡፡ እንዲያውም እንደ አወሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2018 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ብቻ 100 ሚሊየን የሚደርሱ ኣሳማዎች የአፍሪካን ስዋይን ፌቨር በተሰኘው በሽታ ስለመሞታቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የአሳማዎቹ ተረፈ ምርት እና ጽዳጅ በእርሻው ውስጥ ውሃን ለማሞቅ እና ባዮጋዝ ለማመንጨት እንደሚረዳ የተገለጸ ሲሆን ሰራተኞችም ይህንን በመቆጣጠር ላይ ተጠምደው ይስተዋላሉ፡፡
ወደ ጣቢያው የሚገቡ ሰራተኞች ሰዎች ለመግባትም ሆነ ለመውጣት ራሱን የቻለ የንጽህና እና ከቫይረስ የሚጸዱበት ሂደት እና ምስክር ወረቀት መያዝ እንደሚያስፈልግ የእርሻ ጣቢያው ያስገድዳል፡፡
እኤአ በ2022 የሀገሪቱ የአሳማ ምርት ተዋጽኦ በ4 ነጥብ 6 በመቶ መጨመሩን መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን የስጋ ውጤት ምርትም 55 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን ስለመድረሱና በዓለም ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ ሀገራት መሰለፏ ይ ሆኗል፡፡
በዚሁ ዓመት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 784 ሚሊየን አሳማዎች ስለመኖራቸው ሲጠቀስ 452 ነጥብ 6 ሚሊየን አሳማዎች በቻይና ብቻ እንደሚገኙ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በተያያዘም ከ400 በላይ ህንጻዎችን ለአሳማ ማርቢያ በመጠቀም በመላው ቻይና ከፍተኛ የአሳማ ስጋ ለማምረት ስለመሰራቱም ነው የተጠቆመው፡፡

በአውሮፓ 140 ሚሊየን፣ በአሜሪካ 74 ሚሊየን እንዲሁም በብራዚል 35 ሚሊየን ፣ በሩሲያ 26 ሚሊየንና በካናዳ ደግሞ 14 ሚሊየን አሳማዎች እንዳሉ ቁጥራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በ4 ቢሊየን ዩዋን የተገነባው ይህ የአሳማ እርሻው የጋዝ፣ የሙቀት፣ የማቀዝቀዣ እና የመመገቢያ ልዩ መቆጣጠሪያ ያለው ሲሆን 30 ሺ የመመገቢያ ቀዳዳዎች በአንድ የኮምፒውተር መቆጣጠሪያ ክሊክ ብቻ ከከሰው ንክኪ ነጻ ማዕከል ይከፈታሉ፣ ይዘጋሉ፡፡ አሳማዎቹም የሚፈልጉትን ምግብ ይመገባሉ ሲል ዘጋርዲያን በአስገራሚነት አስፍሮታል፡፡
ለአሳማዎቹ ጤንነት በተለይም የተለየ በሽታ ቢከሰት በቀላሉ ሊዛመት ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ቢነሱም እንዲያውም ከዱር እንስሳት ጋር ንክኪ ባለመኖሩ በበሽታ የመጠቃት እድላቸው አነስተኛ ነው ለክትባትና ክትትልም የተሻለና ምቹ ነው ተብሏል፡፡

