በድሬዳዋ የፊት ቆዳን በመንከባከብ በስፋት የሚታወቀው ቀሲል ወይም የቆርቆራ ዛፍ ነው። ፍሬው የሚበላ ሲሆን፣ የቅጠሉ ዱቄት ደግሞ ከውሃ ጋር ሲቀላቀል አረፋ ያወጣል፤ አረፋውም ሳሙናን በመተካት ፊትን ለመታጠብ፣ ቆዳን ለማፅዳት እንዲሁም ለፀጉር እንክብካቤ ይውላል።
ቀሲል በውስጡ የቫይታሚን ሲ ንጥረነገር እንዳለው፣ ፊትን የማፅዳት እና የማፍካት ባሕሪ እንዳለው ነው የምትናገረው። ሌላኛው ምርት የጽጌሬዳ አበባ ውሃ ሲሆን ፊት እርጥበት እንዲኖረውና በተለያዩ ባክቴሪያዎች አማካኝነት ፊት ላይ የሚወጡ እንከኖችን ለመከላከል ይጠቅማል።
ዲክራ ሰኪብ የዚክራ ናቹራል የፊት ቆዳ መንከባከቢያ ምርቶችን ታዘጋጃለች፡፡
በዲክራ ከሌሎች ውሕዶች ጋር ተቀይጦ የሚዘጋጀው በማዕድን የበለጸገ የሸክላ አፈር ይጠቀሳል፤ ይህን ግብዓት በመጠቀም በኩል ግብፅ፣ ሞሮኮ እና አንዳንድ የዓረብ ሀገራት በስፋት እንደሚጠቀሙበት ይጠቀሳል። ይህንን ምርት ከእነዚህ ሀገራት በማስመጣት ከሀገር ውስጥ ዕፅዋቶች ጋር በመደባለቅ ታዘጋጃለች። ‹‹በማዕድን የበለጸገ የሸክላ አፈር በሀገራችን ቢገኝም፣ ለፊት ቆዳ መንከባከቢያነት ለመዋል የተለያዩ ሂደቶችን ማለፍና በባለሙያዎች ተመርምሮ መረጋገጥ እንደሚኖርበትም አስገንዝባለች።
የእርድ ውሕድም ታዘጋጃለች። ከተለያዩ ግብዓቶች ጋር በመደባለቅ የምታዘጋጀው ውሕዱ በፀሐይ ለተጎዳ ፊት፣ ብጉር ላለባቸው ሰዎች እና ፊትን ለማፍካት ያገለግላል።
ፊትን ለማለስለስ የሚውለው የፊት ቅባትም ታዘጋጃለች። ይህንንም ከወይን ፍሬ ዘይት፣ ከአልመንድ ፍሬ እና ከሌሎች ግብዓቶች ነው የምታዘጋጀው። ቅባቱ ፊታችን ላይ የሚገኘውን ተፈጥሯዊ ወዝ የሚተካ መሆኑን ጠቅሳ፣ የተለያዩ ውሕዶችን ከተጠቀምን በኋላ ሊከሰት የሚችለውን ድርቀት ለመከላከል እንደሚጠቅመም ጠቁማለች።
ዲክራ ቀሲል 150 ግራም በ300 ብር እና 300 ግራም በ500 ብር ለገበያ ታቀርባለች። ለደንበኞቿ የምታቀርበው በቆዳቸው አይነት ላይ ምክር ከሰጠች በኋላ ሲሆን በጥቅሉ በሁለት ሺህ 200 ብር የሚሸጠው ግብዓት ለሦስት ወር ያህል እንደሚያገለግልም ገልጻለች።
ቀሲል በየእለቱ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችልና ውሕዶችን የያዘው ጥቅል ደግሞ በሳምንት ለሦስት ቀናት መወሰድ እንዳለበትም ተጠቃሚዎቿን ትመክራለች። (የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት September 25, 2023)
